"ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳን አደረግሁ" መዝ. 88፥3

የራማ ኪዳነምሕረት አመሠራረት፣ አስደናቂ ታሪክ እና የልማት እንቅስቃሴ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳን አደረግሁ” መዝ. 88፥3

የገዳሟ አመሠራረት

ገዳም ማለት በግእዝ ቋንቋ ጫካ አንድም ምድረ በዳ ማለት ሲሆን ድምፀ አራዊት የሚሰማበት፣ ጸብአ አጋንንት የሚያይልበት፣ ግርማ ሌሊት የሰፈነበት፣ ቅዱሳን አባቶች እና እናቶች እነዚህን ሁሉ ታግሰው ጤዛ ልሰው፣ ዳዋ ጥሰው፣ ድንጋይ ተንተርሰው በጾም፣ በጸሎት እና በስግደት በመጽናት ከፈጣሪያቸው ጋር የሚነጋገሩበት ሥፍራ ነው፡፡

 

“ወእምዝ ለእግዚእ ኢየሱስ አዕረጎ መንፈስ ገዳመ ይትመከር እምኀበ ዲያብሎስ፤ ከዚህ በኋላ ጌታ ኢየሱስን በዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ ወደ ገዳም ወሰደው’ ማቴ. 4፥1 እንዲል በገዳም በዓት አጽንቶ መኖርን የመሠረተልን ራሱ ባለቤቱ መድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡

 

በመሆኑም ገዳም በመንፈሳዊ ተጋሎ ታሪክ የሚሠራበት የተባሕትዎ እና የልማት ሥፍራ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሃገራችን በሦስቱ ሕግጋት (በሕገ ልቡና፣ በሕገ ኦሪት እና በሕገ ወንጌል) ጸንታ የኖረች እና ከእስራኤል ቀጥላ ፈጣሪዋን ያወቀች ጥንታዊትና ታሪካዊት ሃገር ነች፡፡

 

ርትዕት የሆነችው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት በደጋጎቹ ነገሥታት በቅዱሳን አብርሃ ወአጽብሐ አማካይነት ብሔራዊት ተብላ ከታወጀችበት ጀምሮ በፈቃደ እግዚአብሔር በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ታንጸዋል፡፡ አብያተ ክርስቲያናትም ገጠር፣ ደብር፣ ገዳም ተብለው ይከፈላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ1ሺህ 200 በላይ ገዳማት እንዳሉ ይገመታል፡፡


ገዳማትን (አብያተ ክርስቲያናትን) የሚጠብቅ የማያንቀላፋው ቸር እረኛና የቤተክርስቲያን ራስ የሆነው መድኃኔዓለም ለጠቢቡ ሰሎሞን “በዚህ ሥፍራ ለሚጸለይ ጸሎት ዓይኖቼ ይገለታሉ ጆሮቼም ያደምጣሉ’ 2ዜና.7፥15 እንዳለው ይህች ምዕራገ ጸሎት እና ምዕራፈ ቅዱሳን ገዳምም እርሱ በፈቀደ በሰሜን ወሎ ሃገረ ስብከት በቆቦ ወረዳ ዞብል አካባቢ ትገኛለች፡፡ ይህች የደብረ ሲና ራማ ኪዳነምሕረት አንድነት ገዳም ቁጥራቸው ከዘጠኙ ቅዱሳን በሆኑት በአባ ጉባ እና በአባ ገሪማ በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከዛሬ 1400 ዓመታት በፊት እንደተመሠረተች ታሪኳ ይነግረናል፡፡

አስደናቂው የገዳሟ ታሪክ በአጭሩ

በ451 ዓ/ም ኬልቄዶን ላይ የነበሩት የጉባዔ ከለባት ተሳታፊዎች መለካውያን መናፍቃን ቅዱስ ዲዮስቆሮስንና ተከታዮቹን ባሳደዱ ጊዜ ከተለያዩ አኅጉራት ተሰዓቱ (ዘጠኙ) ቅዱሳን ወደ ሃገራችን መጥተዋል፡፡ እነዚህም ቅዱሳን የተለያዩ መንፈሳዊ መጻሕፍትን ከልዩ ልዩ ቋንቋዎች ወደ ግእዝ ሲተረጉሙ በርካታ ገዳማትን መሥርተዋል፡፡ ከተሰዓቱ ቅዱሳን መካከል በሚገኙት በአባ ጉባ እና በአባ ገሪማ አማካይነትም የራማ ኪዳነ ምሕረት አንድነት ገዳም ተመሥርታለች፡፡

 

በእነዚህ ቅዱሳን የተመሠረተችው ገዳም በ8ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ የተነሣችው ፈላሻዋ ዮዲት ጉዲት (እሳቶ) እንዲሁም በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በግራኝ አሕመድ ተከታታይ ጥፋት ቢደርስባትም በልዑል እግዚአብሔር ፈቃድ እና ሰማዕቷና ጻድቋ ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ (እመ ምዑዝ) ዳግመኛ አቅንታ እንደገደመቻት ይነገራል፡፡

 

ከዚህም በኋላ ወርቅ በእሳት እንዲፈተን ገዳሟ እና ገዳማውያኑ በመከራው እሳት በየዘመናቱ ተፈትነው ፈተናውንም በሰማዕትነት እየተወጡ ከአጼ ዮሐንስ አራተኛ ዘመነ መንግሥት ደረሰች፡፡  አጼ ዮሐንስም ሃገር በሚያቀኑበት ወቅት በዚህች ሥፍራ ሠራዊታቸውን አስፍረው እንደነበር ይነገራል፡፡ በዚህን ጊዜ አካባቢውን ከሚቆጣጠረው ሠራዊት መካከል አንዱ ወታደር አውሬ ለማደን ወደ ጫካ ውስጥ ሲገባ ወፎች የግምጃ ቅዳጅ በአፋቸውና በእግራቸው ያንጠለጠሉ ሲወጡ ይመለከትና አቅጣጫውን ተከትሎ ሲሄድ ዋሻ ያገኛል፡፡ እገባለሁ ብሎ ሲደፋፈር እንደ እሳት ወላፈን ገርፎ ይጥለዋል፡፡ ወዲያውም አእምሮውን ስቶ ወድቆ ያድራል፡፡ መጥፋቱ ታውቆ ሲፈለግ ከዚያ ወድቆ ተገኝቷል፡፡ አይናገርም፤ አይሰማም ወዲያው በካህናት አማካይነት በጸበልና በጸሎት ሲረዳ አንደበቱ ተፈትቶ ጆሮውም ተከፍቶለት ያየውን መስክሯል፡፡

 

ዋሻውንም ካህናቱ በጸሎት እና በምሕላው ከፍተውት ሲገቡ ታቦተ ኪዳነምሕረትና ሌሎችም ልዩ ልዩ ንዋያተ ቅድሳትና የጥንት ገዳምነቷ ምስክር የሆኑ ሌሎች ቅርሳ ቅርሶች ተገኝተዋል፡፡ በዚህም ከ300 ዓመታት በላይ ተሰውራ በንጹሐኝ ቅዱሳን ስትገለገል የነበረችው ታቦተ ሕግ በፈቃደ እግዚአብሔር ተገለጸች፡፡ አጼ ዮሐንስም እንደ ጥንቱ ገዳምነቷ እንድተጸና አዝዘው ተገደመች፡፡ ከ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ያለማቋረጥ በተአምራት አድራጊነቷ እና በድንቅ ሥራዋ ገዳሟ ከጊዜ ወደ ጊዜ የታወቀች የቅዱሳን መናኸሪያ በመሆን አሁን እስካለንበት ዘመን የደረሰችው ይህች ጥንታዊት ገዳም የታሪክ፣ የምናኔ ቦታ እንደመሆኗ አሁንም ልዩ ልዩ ገቢረ ተአምራት የሚታይባት እና ብዙ መነኮሳትና መነኮሳዪያት በጸሎት በአንድነት ገዳምነት የሚገለገሉባት ለምእመናንም በረከተ ሥጋወነፍስ የምታሰጥ ናት፡፡